Breaking News

የገቢዎች ሚኒስቴር በደቡብ ክልል የገቢ ግብር ንቅናቄ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ

የገቢዎች ሚኒስቴር በደቡብ ክልል የገቢ ግብር ንቅናቄ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

በቅርቡ የተካሄደው የትግራይና አማራ ክልል የገቢ ግብር ንቅናቄ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁንና ውጤታማ ስራ መሰራቱንም ተናግሯል።

በሀገሪቱ ግብር መክፈል ከነበረባቸው ዜጎች መካከል የሚከፍሉት 60 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የተናገሩት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ይህንን ለማሻሻል ሚኒስቴሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ግብር ለሃገሬ በሚል መሪ ቃል በደቡብ ክልል የሚጀመረው የገቢ ግብር ንቅናቄ የካቲት 3 ቀን በሃዋሳ ከተማ ውስጥ በሚካሄድ የሩጫ ውድድር እንደሚጀመር ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ  እንዳሉት ከዚሁ ጎን ለጎን የፓናል ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን እንቅስቃሴውም ህብረተሰቡ በግብር ላይ ያለውን አመለካከት ያሻሽለዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግብር ለሃገሬ በሚል መሪ ቃል የፊታችን የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ታላቅ ሩጫ የሚካሄድ ሲሆን፤ በየካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ የእምዬን ለእምዬ በሚል መሪ ቃል የስዕል እና የሙዚቃ ድግስ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በህብረተሰቡ ዘንድ ደረሰኝ ከመቀበል ጋር በተያያዘ የግንዛቤ ክፍተቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሯ እስካሁን ድረስ በግብር ማጭበርበር ላይ በተደረገ ክትትል ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

 

 

leave a reply