SportSportsWorld

ዛሬ ምሽት የዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

ዛሬ ምሽት የዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

የ2018/19 የዩሮፓ ሊግ የውድድር ዓመት የመዝጊያ የፍፃሜ ግጥሚያ በሁለቱ የእንግሊዝ፤ ጠበብ ሲል ደግሞ የለንደን ከተማ ተቀናቃኝ ክለቦች ቼልሲ እና አርሰናል መካከል ይደረጋል፡፡ all-English Europa League final እንደማለት፡፡

ጨዋታው 70,000 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ባለው የአዘርባጃኑ ባኩ ኦሊምፒክ ስታዲየም ሲደረግ ምሽት 4፡00 ላይ ይጀመራል፡፡  

ሁለቱ የምዕራብ እና የሰሜን ለንደን ክለቦች ከመዲናዋ ለንደን የሚጀመር ከ4ሺ በላይ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው በአዘርባጃኗ መዲና ባኩ የፍፃሜ ግጥሚያውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡

የምሽቱ ጨዋታ ለመድፈኞቹ ያለው ትርጉም ከሰማያዊዎቹ ላቅ ያለ ሲሆን ድል ቢቀናቸው ዋንጫውን ከማሳካታቸው በላይ በፕሪምየር ሊጉ ያላገኙትን የቀጣይ ዓመት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ በአቋራጭ የሚያገኙ ይሆናል፡፡

ሰማያዊዎቹ ግን አስቀድመው የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ያረጋገጡ በመሆኑ ዋንጫውን ቢያገኙ የውድድር ዓመቱን ቢያንስ በዚህ ዋንጫ የሚያጠናቅቁ ይሆናል፡፡

የምዕራብ ለንደኑ አለቃ ማውሪዚዮ ሳሪ ከምሽቱ ግጥሚያ በኋላ አሸነፉም፤ አላሸነፉም ስታንፎርድ ብሪጅን እንደሁ መልቀቃቸው አይቀር እያሉ መገናኛ ብዙሃኑ እየዘገቡ ነው፡፡

ማሲሚሊያኖ አሌግሪ ከዩቬንቱስ አሰልጣኝነታቸው መሰናበታቸውን ተከትሎ ሳሪ ከክለቡ ጋር ስማቸው ተያይዟል፡፡ የ60 ዓመቱ አዛውንት እስካሁን በአሰልጣኝነት ህይወታቸው ትልቅ ዋንጫ ማሳካት አልቻሉም፡፡

በአንፃሩ የአርሰናሉ አሰልጣኝ ኡናይ ኢመሪ የዚህን ውድድር ዋንጫ በስፔን የሲቪያ ቆይታቸው ከ2014 እስከ 2016 ሶስት ዋንጫዎችን አሳክተዋል፡፡

በዚህም ኢመሪ በአውሮፓ ውድድሮች አናሳ ስኬት ያለውን አርሰናል ልምዳቸውን ተጠቅመው ከአህጉራዊ ዋንጫ ጋር ያገናኙት ይሆን የሚለው ይጠበቃል፡፡

ቼልሲ ዩሮፓ ሊግ በ2013 ያሸነፈ ሲሆን አርሰናል ደግሞ የድሮውን የአውሮፓውያን ዋንጫ በ1994 ካነሳ በኋላ በአህጉሩ የዋንጫ ስኬት የለውም፡፡ ኢመሪ ደግሞ የመድፈኞቹን የ25 ዓመት የአህጉራዊ ዋንጫ ናፍቆት ጋር ለመገናኘት ያሉትን ተጫዋቾች በማጀገን የምሽቱን ግጥሚያ በጉጉት ይናፈቃሉ፡፡

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የፈረንሳዩን ፓሪስ ሴንት ዤርማ ሊቀላቀል ይችላል ተብሎ እየተነገረ የሚገኘው ንጎሎ ካንቴ በጨዋታው ለመሰለፍ የመጨረሻ ምርመራ ይደረግለታል ተብሏል፡፡

በሰማያዊዎቹ የዩሮፓ ሊግ የዘንድሮ ጉዞ ሚና የነበራቸው ወጣቶቹ ሩበን ሎፍተስ ቺክ እና ካሉም ሁድሰን ኦዶይ ከፍፃሜ ጨዋታው ውጭ እንደሆኑ ተረጋግጧል፤ የካንቴ አለመኖር ሳሪ የአማካይ ቦታቸው በጆርጊንሆ፣ ማቲዎ ኮቫችች እና ሮዝ ባርክሌይ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ይሆናል፡፡ አማራጭም አይኖራቸው፡፡

በአርሰናል በኩል ሄንሪክ ሚኪታሪያን ሀገሩ አርሜኒያ ከአዘርባጃን ጋር ባላት ፖለቲካዊ አለመግባባት፤ ለደህንነቱ በመስጋቱ ከቡድኑ ጋር አብሮ አልተጓዘም፡፡

አንጋፋው ቼካዊ ግብ ጠባቂ ፒተር ቼክ በእግር ኳስ ህይወቱ የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያደርግ ቢሆንም ተጫዋቹ ከውድድሮቹ መጠናቀቅ በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ቼልሲ በስፖርቲንግ ዳይሬክተርነት ሚና የሚያቀና በመሆኑ ኡናይ ለቼክ የግብ ጠባቂነቱን ቦታ ባይሰጡት የሚለው እየተነሳ ቢሆንም አሰልጣኙ ውሳኔውን ለእኔ ተውልኝና ሌላው እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆኑ አያሰሳስብም እያሉ ነው፡፡

ወደ 70 ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው የባኩ ኦሊምፒክ ስታዲየም የፍፃሜ ተፋላሚ ክለቦች ደጋፊዎች ትኬት የተፈቀደው እያንዳንዳቸው አምስት ሺ ብቻ መሆኑ ክለቦችን እና ደጋፊዎችን አስቆጥቷል፡፡

ተቃውሟቸውንም በተለያዬ መንገድ እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

አርሰናልና ቼልሲ የሚያደርጉት የፍፃሜ ጨዋታ፤ በአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫ አሊያ ዩሮፓ ሊግ የዋንጫ ፍፃሜ ሁለቱም የእንግሊዝ ክለቦች ሲሆኑ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በ1972 በያኔው የማህበረሰብ ዋንጫ ፍፃሜ ቶተንሃም እና ወልቭስ መገናኘት ችለው ነበር፡፡

ለማንኛውም ይሄንን የፍፃሜ ግጥሚያ ጣሊያናዊው አርቢትር ጂያንሉካ ሮቺ ይመሩታል ተብሏል፡፡

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button
Close
Close